ጉቦ በመቀበል የሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የኦዲት ባለሙያዎች ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የድርጅቶችን የግብር መጠን እንቀንሳለን በማለት ከፍተኛ መጠን ያለው ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የአአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ላይ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።
ተጠርጣሪዎቹ የተሰጣቸውን ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተው ከግብር ከፋይ ግለሰቦች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከግብር ከፋይ ድርጅቶች ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ጉቦ በመቀበል ወንጀል ተጠርጥረው በጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን በቀጠሮው ግለሰቦቹ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ስር በማዋል በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ሲያከናውን የቆየውን የመጀመሪያ ዙር የምርመራ ማጣሪያ ስራውን ማጠናቀቁን ለችሎቱ አስታውቋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በመዝገቡ ላይ ተሰይሞ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ መረከቡን ገልጾ፤ መዝገቡ ላይ ለመወሰን በሕጉ መሰረት የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎቹ ላይ 1 ሺህ 620 የሰነድ ማስረጃዎች መሰብሰቡንና በተደረገው ማጣራት ስራ ቤቶችና ተሽከርካሪዎች መገኘታቸውን እንዲሁም 119 ሚሊየን ብር ጥቅም የተገኘና ጉዳት የደረሰ መሆኑን ገልጾ ሰነዶችን ተመልክቶ ለመወሰን ጊዜ እንደሚያስፈልገው አብራርቷል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷ ቀደም ብሎ የምርመራ ስራ መጠናቀቁን ገልጸው በምርመራ ማጣሪያ ስራው ላይ ዐቃቤ ሕግ አብሮ ሲመረምር ቆይቶ እንደ አዲስ መዝገብ ተመልክቼ ለመወሰን ክስ መመስረቻ ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱ ተገቢነት የለውም በማለት ደንበኞቻቸው በእስር ሊቆዩ እንደማይገባ በመግለጽ ተከራክረዋል።
የ3ኛ እና የ6ኛ ተጠርጣሪ ጠበቆች ደንበኞቻቸው የወንጀል ተሳትፎ እንደሌላቸው በመግለጽ ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም በማለትም ተከራክረው ነበር።
የ4ኛ ተጠርጣሪ ጠበቃ በደንበኛው የባንክ ሂሳብ ውስጥ 4 ሚሊየን ብር ማን እንዳስገባላት ሳታውቅ መግባቱን በመጥቀስ እና ከወንጀሉ ጋር የሚያገናኛት ነገር እንደሌለ ተገልጾ የሁለት ወር ህጻን ያላት አራስ መሆኗን ፍርድ ቤቱ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ዋስትና እንዲፈቀድላት ተጠይቋል።
ጠበቆቻቸው የደንበኞቻቸው ዋስትና መብት እንዲከበርም የጠየቁ ሲሆን÷ ዐቃቤ ሕግም የደንበኞች ተሳትፎ አልተለየም ተብሎ ለቀረበ መከራከሪያ መልስ ሰጥቷል፡፡
በዚህም 3ኛ እና 6ኛ ተጠርጣዎች ከፍተኛ የግብር ከፋይ ኦዲተሮች መሆናቸውን ጠቅሶ÷ ግብር እናስቀንሳለን እየተባለ በተሰራ የኦዲት ስራ ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው ገልጾ መልስ ሰጥቷል፡፡
እንዲሁም ዐቃቤ ሕግ 119 ሚሊየን ብር ጥቅም የተገኘበትና ጉዳት የደረሰበት መዝገብ መሆኑን በመግለጽ÷ ክስ ሊመሰረት የሚችለው ዋስትና ሊያስከለክል በሚችል ድንጋጌ ስር እንደሚሆን ጠቅሶ መዝገቡን ተመልክቶ እስኪወስን ተጠርጣሪዎች በእስር እንዲቆዩ ጠይቋል።
የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከ4ኛ ተጠርጣሪ ውጪ ባሉ ተጠርጣዎች ላይ የክስ መመስረቻ ለዐቃቤ ሕግ መፈቀድ እንዳለበት በማመን ለዐቃቤ ሕግ የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል፡፡
4ኛ ተጠርጣሪን በሚመለከት የሁለት ወር ህጻን ልጅ ያላት አራስ መሆኗን ጠቅሶ የህጻኗን ሁኔታ ከግምት በማስገባት በ100 ሺህ ብር ዋስትና ተፈቅዶላታል፡፡
ዐቃቤ ሕግ ለተጠርጣሪዋ ለግብር ማስቀነሻ በሚል ከተለያዩ ድርጅቶች 16 ሚሊየን ብር በሂሳብ ቁጥሯ እንደገባላት ገልጾ ዋስትና መፍቀዱ አግባብ አይደለም በማለት ዋስትናው እንዲታገድለት ጥያቄ አቅርቧል።
በታሪክ አዱኛ