Fana: At a Speed of Life!

በናይጀሪያ የነዳጅ ታንከር ፍንዳታ በተከሰተ የእሳት አደጋ የ94 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜናዊ ናይጀሪያ በነዳጅ ታንከር ፍንዳታ ምክንያት በተከሰተ የእሳት አደጋ የ94 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ።

በናይጀሪያ ጂጋዋ ክልል የተከሰተው አደጋ በተሸከርካሪ ሲጓጓዝ የነበረ የነዳጅ ታንከር በድንገት ፈንድቶ ባስከተለው የእሳት አደጋ ከባድ ጉዳት አስከትሏል።

በዚህም ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 50 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በአካባቢው በሚገኝ የጤና ተቋም ህክምና እያገኙ እንደሆነ ተገልጿል።

አደጋው የደረሰበት ተሽከርካሪን ጨምሮ በርካታ ንብረት መውደሙም ተነግሯል።

ከነዳጅ ታንከሩ ፍንዳታ በኋላ የአካባቢው ሰው ወደ አደጋው ስፍራ እንዳይጠጋ ፖሊስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በመጣስ ሰዎች ወደ አደጋው ስፍራ መጠጋታቸው ጉዳቱን ከፍ እንዳደረገው ተመላክቷል፡፡

የጅጋዋ ፖሊስ ቃል አቀባይ ላዋል ሽሱ አዳም÷ አደጋው ነዳጅ የጫነው ተሸከርካሪ ከካኖ ወደ ዮቤ ግዛት እየተጓዘ በነበረበት ወቅት ተሸከርካሪው ከሾፌሩ ቁጥጥር ውጭ በመሆኑ የተከሰተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአደጋው ሾፌሩ ጉዳት እንዳልደረሰበት የተገለፀ ሲሆን ለተጨማሪ ምርመራ ወደ እስር ቤት መወሰዱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ባለፈው መስከረም ወር በናይጀሪያ ኒጀር ግዛት ነዳጅ ጫኝ መኪና የቀንድ ከብት ከጫነ መኪና ጋር በመጋጨቱ 59 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.