የአልዌሮ ግድብን በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት ይሰራል – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ እና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የአልዌሮ ግድብን ጎብኝተዋል።
ከዓመታት በፊት በጋምቤላ ክልል አቦቦ ወረዳ የተገነባው የአልዌሮ ግድብ ከ10 ሺህ ሄከታር መሬት በላይ ማልማት የሚችል አቅም ቢኖረውም የታቀደለትን ያህል ሳያገለግል መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡
አብርሃም በላይ (ዶ/ር)÷ እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ የታቀደውን አቅድ ለማሳካት የተለያዩ የመስኖ አማራጮችን ተጠቅሞ ዓመቱን ሙሉ ማመረት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ለረጅም ዓመታት ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየውን የአልዌሮ ግድብ በሙሉ አቅም ወደ ስራ ለማስገባት በጥናት ላይ የተመረኮዙ ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ክልሉ ሰፋፊ እርሻዎችና ለም መሬት ያሉት በመሆኑ የመስኖ አማራጮችን በማስፋት ዓመቱን ሙሉ ማምረት ወደሚችልበት አሰራር እንዲሸጋገር በቅንጅት እንደሚሰራ አስረድተዋል።
ወ/ሮ አለሚ በበኩላቸው÷በክልሉ ያለውን የእርሻ መሬትና የውሃ ሃብት በተገቢው መንገድ ለማልማት ማህበረሰቡን እና ባለሃብቶችን ያሳተፈ የልማት ስራ ይሰራል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በተለይም አልዌሮን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የተጀመሩ ለመስኖ ስራ አመቺ የሆኑ ወንዞችን በጥናት በመደገፍ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።