በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከመኸር እርሻ 29 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ2017 ዓ.ም የመኸር እርሻ 680 ሺህ ሔክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ሃላፊ አቶ ሃይለማሪያም ተስፋዬ÷ በክልሉ በመኸር እርሻ ከለማው ሰብል 29 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በሰብል ከተሸፈነው ውስጥ 144 ሺህ ሔክታር ማሳ ጤፍ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው÷ 147 ሺህ ሔክታር ማሳ ደግሞ በኩታ ገጠም እርሻ እየለማ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የክልሉ መንግስት ለፍራፍሬ ልማት ሥራ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ በመኸር እርሻ 87 ሺህ ሔክታር ማሳ በፍራፍሬ መሸፈኑን ጠቅሰዋል፡፡
አርሶ አደሮች ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ፣ ከውጭ የሚገቡ የሰብል ምርቶችን በራስ ምርት እንዲተኩና የሥራ እድል እንዲፈጥሩ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡