የብሪክስ ፕላስ የመረጃና እና የባህል ሚዲያ ማዕከል ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪክስ ፕላስ የመረጃ እና የባህል ሚዲያ ማዕከል መመስረቱን አስመልክቶ የመክፈቻ መርሐ ግብር ዛሬ በሩሲያ ሞስኮ ተካሂዷል፡፡
ማዕከሉ በብሪክስ ፕላስ አባል ሀገራት መካከል የሰብዓዊ ትብብርን ለማጎልበት፣ ባህልን፣ ሳይንስን እና ትምህርትን ለማስተዋወቅ ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡
በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ ከኢትዮጵያ፣ ብራዚል፣ ግብፅ፣ ህንድ፣ ኢራን፣ ቻይና፣ ኩባ፣ ሩሲያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቱርክ እና ደቡብ አፍሪካ የተውጣጡ የመንግስት አካላት፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ÷የማዕከሉ መመስረት በብሪክስ አባል ሀገራት ውስጥ ባሉ ሚዲያዎች መካከል የባህል እና የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
“በዚህ ጉዞ ውስጥ ታሪክን በማስተዋወቅ እና ልዩነቶችን በማክበር ለአንድ አላማ እንድንሰበሰብ በማስቻል በኩል የመገናኛ ብዙሃን ሚና የጎላ ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ይህንን አጋጣሚ የባህል ግንኙነታችንን ለማሻሻል እና ጠንካራ የብሪክስ ማህበረሰብን ለመፍጠር እንጠቀምበት፤ በጋራ በመንቀሳቀስ በዓለም ላይ ተፅዕኖ መፍጠር እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው አያይዘውም ኢትዮጵያ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2019 ጀምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን የቱሪስት መደረሻዎችን መገንባቷን ጠቅሰው፤ለአብነትም በአዲስ አበባ የአንድነት ፓርክ እና እንጦጦ፣ ከአዲስ አበባ ውጭ ደግሞ ወንጪ፣ ጎረጎራ እና ሃላላ ኬላን አንስተዋል፡፡
እነዚህን ስፍራዎች ደረጃቸውን በጠመቁ መሰረተ ልማቶች በማልማት የተፈጥሮ ቅርሶችን ከመጠበቅ ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ዘላቂ ልማት አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዕለቱ የሚዲያ ሚና ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይትም መካሄዱን የቲቪ ብሪክስ መረጃ ያመላክታል፡፡