Fana: At a Speed of Life!

ከ5 ቢሊየን ብር በላይ በጀት የተመደበለት የአደጋ ሥጋት አስተዳደር ሥርዓት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)በተለያዩ ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግና ከ5 ቢሊየን ብር በላይ በጀት የተመደበለት የአደጋ ሥጋት አስተዳደር ሥርዓት ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ በጀት ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት የተመደበ ሲሆን ÷ለፕሮጀክቱ ትግበራ ኮሚሽኑ ከድርጅቱ ጋር ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ የውል ስምምነት ተፈራርሟል።

በዚህ ወቅት የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በዘጠኝ ክልሎች ባሉ 120 ወረዳዎች ተግባራዊ ይደረጋል።

ይፋ የተደረገው የአደጋ ሥጋት አስተዳደር ስርዓት ፕሮጀክት ከ14 ሚሊየን በላይ ወገኖችን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአደጋ ስጋት ችግሮችን ሀገር በቀል በሆነ መንገድ ቀድሞ መፍታት የሚያስችልና የአደጋ ስጋት ቅነሳ አመራር ስርዓትን የሚያጠናክር እንዲሁም ሌሎች በርካታ ፋይዳዎች እንዳሉት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳይ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ ከወንድበላይ በበኩላቸው÷ አምስት ዓመት ለሚቆየው ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ከድርጅቱ መመደቡን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በተለይ ሀገሪቱ የአደጋ ስጋት ዝግጅት፣ የምላሽና የትንበያ አቅም እንዲሁም የውስጥ ሀብትን አቀናጅቶ መጠቀም በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.