Fana: At a Speed of Life!

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ዕጩ ሆነች

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊቷ ናኦሚ ግርማ የ10ኛው ዙር የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ዕጩ ውስጥ ገብታለች።

በ20 አመታቸው ወደ አሜሪካ ካቀኑ ኢትዮጵያውያን እናትና አባት የተወለደችው የ24 ዓመቷ ናኦሚ የአሜሪካ ምርጥ ተጫዋች ተብላ የተመረጠች የመጀመሪያዋ ተከላካይ ናት።

የዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የኦሊምፒክ ወርቅ ባለቤት ሲሆን÷ ናኦሚ እያንዳንዱን ደቂቃ ተጫውታለች።

የኋላ ደጀን የምትባለው ናኦሚ ኳስ በመቆጣጠርና በመሪነት ችሎታዋ አድናቆት ይጎርፍላታል።

በሷ የጎላ አስተዋፅዖም የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ወርቅ፣ ኮንካካፍ ጎልድ ዋንጫና ሺ ቢሊቭስ የተባለው ዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል።

ናኦሚ በክለብም ዋንጫ ያልተለያት ሲሆን÷ ከቡድኗ ሳንዲየጎ ዌቭ ጋር የኤን ደብሊው ኤስ ኤል እና የቻሌንጅ ዋንጫዎችን ማንሳቷን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

አሁን ላይም ናኦሚ የቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ዕጩ ሆናለች፡፡

አድናቂዎቿም እስከ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ድምፃቸውን መስጠት እንደሚችሉ የተገለፀ ሲሆን÷አሸናፊዋ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ እንደምትደረግ ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.