ኢትዮጵያ ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን አስጠልላለች- ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት የገቡ ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞች ማስጠለሏን ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ ከኤደንብራ ደቸስ ልዕልት ሶፊ ሔለን ጆንስ ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በወቅታዊ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ የእናቶች ሥነ-ተዋልዶ ጤና እንዲሁም በግጭት ወቅት የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይም መክረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት የገቡ ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን አስጠልላ እንደምትገኝም ፕሬዚዳንት ታዬ ለልዕልቷ አስረድተዋል፡፡
ልዕልት ሶፊ ሔለን ጆንስ በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የምታደርገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ከብሪታኒያ ንጉሥ ቻርለስ 3ኛ ለፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የተላከውን የእንኳን ደስ አለዎት የደስታ መግለጫ መልዕክትም ልዕልቷ አድርሰዋል፡፡