ፕሬዚዳንት ታዬ አውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ አውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ ከአውሮፓ ኅብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ጋር በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት በሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ÷ እየተተገበረ ባለው የኢኮኖሚ ማሻሻያም አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን እንዳብራሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸዋል፡፡
በአውሮፓ ኅብረት በኩል የሚደረጉ ድጋፎች አስፈላጊ መሆናቸውን በማስገንዘብ÷ በኅብረቱ ሊደረግ የሚችለው ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ኮሚሽነሯ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ለተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኅብረቱ እውቅና እንደሚሰጥ እና እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረትን አጋርነት በይበልጥ ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ መስማማታቸው ተገልጿል፡፡