ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከማንቼስተር ዩናይትድ አምባሳደርነት ሊነሱ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የማንቼስተር ዩናይትድ የቀድሞው ስኬታማ አሰልጣኝና ባለፉት ዓመታት የቡድኑ ዓለም አቀፍ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በዓመቱ መጨረሻ ከኃላፊነታቸው እንደሚሰናበቱ ተሰምቷል፡፡
ሰር አሌክስ ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ ቀያይ ሰይጣኖቹን በዓለም አቀፍ አምባሳደርነት እንዲሁም ክለቡን በዳይሬክተርነት በማገልገላቸው በርካታ ሚሊየን ፓውንድ እንደተከፈላቸውም ተገልጿል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ለእርሳቸው የሚከፍለውን ገንዘብ በማስቀረት ማንቼስተር ዩናይትድን ለማደራጀትና ለማጠናከር እንዲውል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ሰር አሌክስ ከኃላፊነታቸው የሚሰናበቱት፡፡
ለዚህም የክለቡ ባለድርሻ የሆኑት ሰር ጂም ራትክሊፍ እና ሰር አሌክስ በጉዳዩ ላይ ተነጋገርው የጋራ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል ተብሏል፡፡
የ82 ዓመቱ ስኮትላንዳዊ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን÷ 13 የፕሪሚር ሊግ፣ 2 የሻምፒዮንስ ሊግ እና 5 የኤፍ ኤ ዋንጫዎችን ለማንቼስተር ዩናይትድ ገቢ በማድረግ በታሪክ የክለቡ ስኬታማው አሰልጣኝ ናቸው፡፡