Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካን የገጠማት የጸጥታና ደህንት ስጋት መፍትሔ ይፈልጋል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ አሁን ላይ የገጠማት አሳሳቢ የጸጥታና ደህንት ስጋት ከውይይት ባሻገር መፍትሔ ይፈልጋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

”አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመድረኩ ተገኝተው÷ አፍሪካ አሁን ላይ አሳሳቢ የጸጥታና ደህንት ስጋት ውስጥ ገብታለች ብለዋል።

በአህጉራችን ጥልቅ የደህንነት ፈተናዎች እያጋጠመ ይገኛል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የውስጥ ግጭቶች፣ ድንበር ዘለል ውጥረቶች እና የሽብር ተግባራትን ማስወገድ በፍጹም አልተቻለም ሲሉ ነው የገለጹት።

አሁን ላይ ወደ ሰላምና መረጋጋት የመጡ ሀገራትም ቢሆን አዳዲስ ውጥረት እያጋጠማቸው ይገኛል በማለት አስገንዝበዋል።

ይህን ተከትሎ የሽብር ቡድኖች ሰላማዊ ወደ ነበሩ አካባቢዎች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ገልጸው፤ እነዚህን ከባድ ተግዳሮቶች ከውይይት የተሻገረ መፍትሔ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።

የጉባኤው ዓላማም ለዚህና መሰል ተግዳሮቶች በመወያየት የጋራ መፍትሄ ማምጣትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ላደረገችው ያልተቆራረጠ አበርክቶ በአፍሪካ ህብረት በኩል አድናቆት ተችሯታል፡፡

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.