ሆስፒታሉ ከአዕምሮ በተጨማሪ ሌሎች የተሟሉ ሕክምናዎችን ለመስጠት እየተዘጋጀሁ ነው አለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከአዕምሮ ሕክምና በተጨማሪ ለታካሚዎች የተሟላ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ሆስፒታሉ ላለፉት 85 ዓመታት ሕብረተሰቡን ሲያገለግል መቆየቱን የገለጹት የሆስፒታሉ የሕክምና ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ኃይሌ÷ ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ የባለሙያ ስብጥርና የሕክምና ግብዓቶችን እያሟላ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ላይም በድንገተኛ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ በ239 አልጋዎች የአስተኝቶ ሕክምናና በቀን በአማካይ 500 ታካሚዎች በተመላላሽ ሕክምና እያገኙ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የሆስፒታሉ ታካሚዎች ከአዕምሮ ሕክምና ውጭ ተጨማሪ የጤና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሌሎች የጤና ተቋማት በመሄድ ሲገለገሉ መቆየታቸውን አስታውሰው÷ አሁን ላይ ተቋሙ አድማሱን በማስፋት ለታካሚዎች የተሟላ ሕክምና ለመስጠት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም የባለሙያዎች ቅጥርና የሕንጻ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው÷ እስከ ጥር 2017 ዓ.ም ድረስ በሆስፒታሉ የተሟላ አገልግሎት ለመጀመር መታቀዱን አመላክተዋል፡፡
በቀጣይም ለአካባቢው ሕብረተሰብ የተሟላ ሕክምና የመስጠት ውጥን መያዙን ጠቅሰው÷ ዕቅዱን ለማሳካት የሚያስችል ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ አካላት ከሆስፒታሉ ጋር ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።