Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ኀብረት በቀጣናው ለሚደረገው የፀረ-ሽብር ዘመቻ ድጋፉን እንደሚቀጥል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኀብረት በቀጣናው ለሚደረገው የፀረ-ሽብር ዘመቻ ድጋፉን እንደሚቀጥል በአውሮፓ ኀብረት የውጭ ጉዳይ አገልግሎት የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሪታ ላራንጂና ተናገሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከአውሮፓ ኀብረት የውጭ ጉዳይ አገልግሎት የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሪታ ላራንጂና ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ከኀብረቱ ጋር ስትራቴጂክ አጋርነት ያላት መሆኑን ገልጸው÷በቀጣይም ሁለንተናዊ ግንኙነቷን ለማጠናከር እንደምትፈልግ ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተም ገለጻ ያደረጉ ሲሆን÷የአውሮፓ ኀብረት የፀረ-ሽብር ዘመቻ ዋና አጋር ሆኖ የዘለቀ መሆኑን በማንሳት በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሚደረገውን ፀረ -ሽብር ዘመቻ ትኩረት ሰጥታ እንደምትመለከተው እና በኢትዮጵያ እና በሌሎች ወታደር ባዋጡ ሀገራት መስዋዕትነት የተገኘው ሰላምና መረጋጋት እንዳይቀለበስ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል።

በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለንግድ እና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን በመግለጽ የኀብረቱ አባል ሀገራት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አምባሳደር ሪታ ላራንጂና በበኩላቸው÷ኀብረቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት የምትወጣውን ጉልህ ሚና እንደሚገነዘብ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ኀብረት ከኢትዮጵያ ጋር ላለው ግንኙነት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ በቀጣናው ለሚደረገው ፀረ-ሽብር ዘመቻ ኀብረቱ ድጋፉን እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የአውሮፓ ኀብረት ኢትዮጵያ እያሳየች ያለውን ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚያደንቅ እና በኀብረቱ አባል አገራት ኩባንያዎች እና በኢትዮጵያ ንግድ ማኀበረሰብ መካከል ያለው ትስስር የበለጠ እንዲጠናከር እንደሚሰሩም ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.