Fana: At a Speed of Life!

በመተከልና አዊ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን ሰላም ማስከበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል እና በአማራ ክልል አዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ ለመከላከል ያለመ ውይይት በግልገል በለስ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ ከፍተኛ የጸጥታ አካላት እና የሁለቱ ዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሹቱ÷የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ የሁለቱ የጸጥታ አካላት እና አመራሩ ከመቼውም በላይ በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በቀጣናው የሚስተዋለውን ችግር ለማስወገድ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በጋራ በመወሰን የሕብረተሰቡን ወጥቶ የመግባት መብት ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቴዎድሮስ እንዳለ በበኩላቸው÷ የሁለቱ ዞን አዋሳኝ አካባቢ ህዝቦች ለዘመናት የጋራ እሴት ገንብተው የሚኖሩ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

ይህን አንድነትና አብሮነት የማይመቻቸው አካላት የሚፈጥሩትን ግጭት በዘላቂነት ማስወገድ የሚቻለው በጋራ በመቆም እንደሆነ አጽንኦት መስጠታቸውን የመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል መንገሻ ታከለ÷የጦር መሳሪያ ዝውውርን ጨምሮ የህብረተሰቡን አብሮነት የሚለያዩ አጀንዳዎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ለማስወገድ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.