የቅባት እህሎች እና የጥራጥሬ ምርቶች የቀጥታ ግብይት መመሪያ ጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቅባት እህሎች እና የጥራጥሬ ምርቶች የቀጥታ ግብይት መመሪያ ቁጥር1026/2017 መጽደቁን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
በ2017 የበጀት ዓመት የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች የወጪ ንግድ አፈፃፀምን በማሻሻል ከንዑስ ዘርፉ የወጪ ንግድ ከ750 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማስገኘት ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ይህንን ጥረት ሊያግዝ የሚያስችል የቅባት እህሎች እና የጥራጥሬ ምርቶች የቀጥታ ግብይት መመሪያ ቁጥር 1026/2017 መጽደቁንም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
መመሪያው በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ የግብይት ማነቆዎችን ከመፍታት ባሻገር ወጪን በመቀነስ፣ ተደራሽነትን በማሻሻል እና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን እንደሚያረጋግጥም ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም ላኪዎች ምቹ ሁኔታውን በመጠቀም ምርት እንዲገዙና እንዲልኩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡