ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የፓርላማ ኅብረት ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑክ በጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው 149ኛው ዓለም አቀፍ የፓርላማ ኅብረት ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡
ጉባዔው÷ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን፣ ሰላምና ፀጥታን በማስፈን እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አሥተዳደርን ማጎልበት በሚሉ ዐበይት ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ሀገራት ለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች መፍትሔ ለማመላከት እና በፓርላማ ደረጃ ሊተገበሩ የሚችሉ የትብብር መፍትሔዎችን ለመፈተሽ በሚያስችሉ አጀንዳዎች ላይ ምክክር ይደረጋል መባሉን በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ተሳትፎም ሀገሪቱ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ትብብሯን በይበልጥ ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው የተባለው፡፡
የልዑካን ቡድኑ በቆይታው በዘርፉ የኢትዮጵያን ልምድ በተመለከተ ተሞክሮውን እንደሚያካፍል ተጠቁሟል፡፡
ዓለም አቀፉ የፓርላማ ኅብረት ጉባዔ በዓለም ዙሪያ ላሉ የፓርላማ አባላት ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለመወያየት እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር መድረክ ነው፡፡