ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል ከባለድርሻ አካላት ጋር የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ ማካሄድ ጀመረ።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደቱ በክልሉ ከ104 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከ3 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በመክፈቻው ወቅት እንደገለጹት፥ እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ላለመግባባቶች ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ከምንጫቸው በሀቅና በእውነት በመለየትና አጀንዳ ቀርፆ ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ ለመድረስ ታሪክ የምንጽፍበት ሒደት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በሶማሌ ክልል ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ተከታታይ ቀናት የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ በጅግጅጋ፣ ጎዴ እና ዶሎ አዶ ከተሞች እንደሚካሄድ መጠቀሱን ኢዜአ ዘግቧል።