የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የፍትሕ፣ የአንድነት፣ የእኩልነትና የአርበኝነት መገለጫ ነው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የፍትሕ፣ የአንድነት፣ የእኩልነትና የአርበኝነት ኅብረብሔራዊ መገለጫ ምልክት ነው ሲሉ በም/ ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
17ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት እየተከበረ ይገኛል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞችም አቶ አደም ፋራህ በተገኙበት ዕለቱን የሠንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ-ስርዓት በማካሄድ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።
በዚሁ ጊዜ አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት፥ ሰንደቅ ዓላማ ወሳኝ ሀገራዊ የሉዓላዊነት አሰባሳቢ ምልክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማም የፍትሕ፣ የአንድነት፣ የእኩልነትና ለሀገር ሉዓላዊነት የሚከፈል የአርበኝነትና የኅብረብሔራዊ አንድነት መገለጫ ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
ለሠንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር መስጠት ማለትም የሀገርን ሉዓላዊ አንድነት ለማስጠበቅ ውድ ዋጋ ለከፈሉና ለሚከፍሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት እንዲሁም ቀደምት ጀግኖች አርበኞችን ማክበር እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚተጉ ብርቱ ክንዶችን ማክበርም ሌላኛው የሀገር ምልክት የሆነውን ሠንደቅ ዓላማ ማክበር መሆኑን አንስተዋል።
በሌላ መልኩም ለሀገራቸው ሉዓላዊ ምልክት ክብር መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን በማሰብ ለኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ የተከፈለውን ውድ ዋጋ በማስተማር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።