ሰንደቅ አላማ የህብረት ማሳያ፣ የዜጎች ሀገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት መገለጫ ምልክት ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰንደቅ አላማ የብሔራዊ ህብረትና አንድነት ማሳያ፣ የዜጎች ሀገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት መገለጫ፣ ታሪካዊና ማህበራዊ ትስስር የሚንጸባረቅበት ምልክት ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡
በአከባበሩ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ አባት አርበኞች፣ የመከላከያ ‘ራዊት እና ሌሎች የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ÷ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ የብሔራዊ ህብረትና አንድነት ማሳያ፣ የዜጎች ሀገራዊ ፍቅርና ብሄራዊ ስሜት መገለጫ ታካዊ ማህበራዊ ትስስር የሚንጸባረቅበት ምልክት ነው ብለዋል፡፡
ሰንደቅ አላማ የመስዋትነት፣ የነጻነት፣ የሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አርማም መሆኑን በመግለጽ የአብሮነታችን አርማ ምልክት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደምና አጥንታቸውን ከስክሰው፣ የህይወት መስዋትነት ከፍለው በክብር አስጠብቀው በክብር ያስረከቡን በልባችን ታትሞ የቆዬ የአሸናፊነትና የነጻነት አርማችን ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ ዓመታት ነጻነቷን አስጠብቃ ታፍራ እና ተከብራ የቆየች ታላቅ አፍሪካዊ ሀገር መሆኗንም አንስተዋል፡፡
በየዘመናቱ በተደጋጋሚ የመጡ የውጭ ወራሪ ሃይሎችን እናት አባቶቻችን በአንድነት ቆመው መክተውና አሳፍረው የመለሱት ለኢትዮጵያና ለሰንደቅ አላማ ከሚሰጡት ክብር በመነሳት ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በኢትዮጵያውያን ብቻ ታትሞ የቆየ ብሔራዊ መለያ ብቻ እንዳልሆነ አስታውሰው፤ በአፍሪካውያን እና በጥቁር ህዝቦች ዘንድ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የነጻነትና የእኩልነት ንቅናቄ አርማ ምልክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በየሻምበል ምሕረት