ሰንደቅ ዓላማችን ፀንቶ የቀጠለው ኢትዮጵያውያን በከፈሉት መስዋዕትነት ነው – ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገራችን ሉዓላዊነት ምልክት የሆነው ሰንደቅ ዓላማችን ፀንቶ የቀጠለው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በከፈሉት መስዋዕትነት ነው ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሐሳብ በጋምቤላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሯ በአከባበሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሉዓላዊነታችን ምልክት፣ የነፃነታችን ዓርማና የክብራችን መገለጫ ነው ብለዋል።
ሰንደቅ ዓላማችን ከትውልድ ትውልድ የተሸጋገረ፣ የጀግኖች አባቶቻችን የደማቸው ፍሳሽ እንዲሁም የመስዋዕትነት ውጤት የሆነ የድል ሰንደቅ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ፣ የሕዝቦችን ነፃነትና ክብር ለማጽናት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ ዓላማችን ፍቅርና ክብር በአንድነት መስዋትነት ከፍለዋል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡