ሂዝቦላህ በእስራኤል ወታደራዊ ካምፕ ላይ በፈፀመው ጥቃት ወታደሮች ተገደሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሂዝቦላህ በእስራኤል ወታደራዊ ካምፕ ላይ በፈፀመው የድሮን ጥቃት አራት የእስራኤል ወታደሮች መገደላቸው ተገለፀ፡፡
ትናንት ምሽት በእስራኤል ደቡባዊ ሀይፋ በሚገኘው ቤኒያሚና ወታደራዊ ካምፕ በጎላኒ ብርጌድ ወታደሮች ላይ በተፈፀመ ጥቃት አራት ሲሞቱ ከ50 በላይ የእስራኤል ወታደሮች መቁሰላቸው ተመላክቷል፡፡
ጥቃቱ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ዘመቻ ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ ሂዝቦላህ በእስራኤል ወታደሮች ላይ የፈፀመው ከባዱ ጥቃት መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ፤ የሂዝቦላህ ድሮኖች የእስራኤልን የአየር መከላከያዎችን አልፈው ጥቃቱን ማድረሳቸውን አረጋግጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትናንትናው ዕለት እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 51 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
ከእነዚህ በተጨማሪ 174 ሰዎች በጥቃቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢቢሲ እና አር ቲ ዘግበዋል፡፡