Fana: At a Speed of Life!

የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ኃላፊነታችንን ለመወጣት ቃላችንን በማደስ መሆን አለበት – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ሉዓላዊነታችንን ለማፅናትና የሰንደቅ ዓላማችንን ክብር ከፍ ለማድረግ በሁሉም መስክ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ዳግም ቃላችንን በማደስ መሆን አለበት ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

አገልግሎቱ ለ17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በመልዕክቱም÷ በደምና አጥንት ተጠብቆ የቆየውን የሰንደቅ ዓላማችን ክብርና ሉዓላዊነታችንን ይበልጥ ማፅናት የሚቻለው በተሰማራንበት የሥራ መስክ ተግባራችንን በትጋት ስንከውን እና የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ስንታትር ነው ብሏል፡፡

በተጨማሪም ሌብነትና ብልሹ አሠራሮችን በዓርበኝነት ስሜት ስንዋጋ፣ ሰላማችንን አጽንተን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ስናረጋግጥ እንዲሁም በኅብር ተናብበን መኖር ስንችል መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም ብሏል አገልግሎቱ ባስተላለፈው መልዕክት፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለ17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ያስተላለፈው የመልካም ምኞት መግለጫ ሙሉ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል፡-

እንኳን ለ17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳችሁ!

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፤ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ ለ17ኛ ጊዜ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ይከበራል፡፡

ዕለቱን በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቆመን ስናከብር ያለውን ትርጉምና ክብር በአግባቡ በመረዳት ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የጋራ ዓርማ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነታችን ምልክት፣ የጥንካሬያችን ሐውልት፣ የድላችን ዓርማ፣ የሉዓላዊነታችን መገለጫ እንዲሁም የኅብረ ብሔራዊ አብሮነታችን ዋስትና መሆኑን በአግባቡ በመረዳት ተገቢውን ክብርና ፍቅር መስጠት ይገባል፡፡

ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ረቂቅና ዋጋውም የላቀ ነው። ኢትዮጵያውያን በደረሱበት የዓለም ክፍሎች ይዘውት የሚጓዙት ትልቁ ስንቅና ትጥቅ በልባቸው የተሳለው የሰንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር ነው።

ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቧቸው ስኬቶችና ድሎች ምሥጢሩ ከሰንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር ጋር የተቆራኘ ነው። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የቅኝ ግዛት ቀንበር መስበሪያ፣ የአፍሪካ የነጻነት ምልክትም ነው፡፡

ሰንደቅ ዓላማችን ክብሩና ዝናው ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ኢትዮጵያውን ዛሬም ሆነ ነገ እንደ ትናንቱ መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ናቸው፡፡ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰንደቅ ዓላማው እንዳትደፈርና የሀገሩ ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በጦር ሜዳ አጥንቱን የሚከሰክሰው፣ ደሙን የሚያፈስሰው ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ነው።

በደምና አጥንት ተጠብቆ የቆየውን የሰንደቅ ዓላማችን ክብርና ሉዓላዊነታችንን ይበልጥ ማፅናት የሚቻለው በተሰማራንበት የሥራ መስክ ተግባራችንን በትጋት ስንከውን፣ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ስንታትር፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራሮችን በዓርበኝነት ስሜት ስንዋጋ፣ ሰላማችንን አጽንተን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ስናረጋግጥ እንዲሁም በኅብር ተናብበን መኖር ስንችል መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም።

በምግብ ራሱን የማይችል ሕዝብና ሀገር ሉዓላዊነቱ በተሟላ ሁኔታ ተረጋግጧል ማለት አይቻልም። ይህ የሚረጋገጠው ሁሉም በተሰማራበት መስክ ተግቶ ሲሰራ ብቻ ነው። በመሆኑም የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ሉዓላዊነታችንን ለማፅናትና የሰንደቅ ዓላማችንን ክብር ከፍ ለማድረግ በሁሉም መስክ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ዳግም ቃላችንን በማደስ መሆን አለበት።

“ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፤ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ”

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.