Fana: At a Speed of Life!

በአዋሽ ፈንታሌ ዛሬ ጠዋት ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ከጠዋቱ 1 ሠዓት ከ37 ገደማ በአዋሽ ፈንታሌ በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 6 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ሠመራ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት አደም አሊ ጉዳዩን አስመልክተው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ዛሬ ጠዋት በአዋሽ ፈንታሌ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እስከ አሁን የተለየ ጉዳት የለም፡፡

ቀደም ሲል በፈንታሌ ዛሬ ጠዋት ደግሞ በአዋሽ ፈንታሌ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን በመግለጽ÷ የሚመለከታቸው አካላት በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ሥራ እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ዘርፉ የሚመለከታቸው ድርጅቶች በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ጥናት በማካሄድ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ሣይንሳዊ ግኝቶችን ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምድር ጥናት መምህር የሆኑት ኖራ የኒሞኖ በበኩላቸው÷ አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ዛሬ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 6 መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሕብረተሰቡ አኗኗር ጋር በተያያዘ ጉዳት እንዳይደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ቢሆንም÷ ባለፈው ሣምንት እና ዛሬ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሙያው አጠራር “መካከለኛ ደረጃ” የሚባሉ በመሆኑ የከፋ ጉዳት እና አስጊ ሁኔታ የለውም ብለዋል፡፡

በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥም በከፊል አዲስ አበባን ጨምሮ እስከ አዳማ፣ አዋሽ እና ሌሎች አካባቢዎች ንዝረት መሠማቱን ጠቅሰዋል፡፡

ቀደም ሲል በፈንታሌ ተከስቶ የነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 9 እንደነበር አስታውሰው ዛሬ ጠዋት ላይ የተከሰተው ከዚህ ያነሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.