በባቡር ትራንስፖርት ለሚደርስ ጉዳት የሚከፈለው ካሳ በህግ አግባብ ብቻ እንዲፈጸም ስምምነት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በባቡር ትራንስፖርት ለሚደርስ ጉዳት የሚከፈለው ካሳ የባቡር ትራንስፖርት አዋጅ በሚፈቅደው መሰረት ብቻ እንዲፈጸም ከስምምነት መደረሱን የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ገለጹ።
ዋና ስራ አስፈጻሚው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ የባቡር መስመር የሚያቋርጣቸው የኢትዮጵያ ክልሎች ንብረት ወይም ተንቅሳቃሽ ነገር ተገጨ ተብሎ ካሳ የተከፈለበት ግዜ በታሪክ አልተመዘገበም፣ በህግም አልተደነገገም ብለዋል።
ነገር ግን ባለፉት ጥቂት አመታት የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር አክሲዮን ማህበር ብዙ ሚሊየን ብር አላስፈላጊ በሆነ አግባብ ካሳ ሲከፍል ቆይቷል ሲሉ ገልጸዋል።
ይህንን ተገቢ ያልሆነ የካሳ ክፍያ ለማቆምና በህግ አግባብ ለመፈጸም የሚያስችል ውይይት ከየክልሉ አመራሮች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም በድሬዳዋ አስተዳደር፣ በአፋር፣ ሱማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ተገቢ ያልሆነ የካሳ ክፍያ ለማቆምና የባቡር ትራንስፖርት አዋጅ በሚፈቅደው መሰረት ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ ከስምምነት መደረሱን አመልክተዋል።