Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ የሸቤልለይ ሪዞርትን የግንባታ ሒደት ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አካል የሆነውን የሸቤልለይ ሪዞርት ግንባታ ሒደት ጎብኝተዋል፡፡

አቶ አደም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደገለጹት÷ከጅግጅጋ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በፋፈን ዞን ሸቤልለይ ወረዳ የተጀመረው የሸቤልለይ ሪዞርት ግንባታ 10 ወራትን አስቆጥሯል፡፡

ሪዞርቱ በውስጡ ለቱሪስት መስህብ የሚያገለግሉ 8 ዘመናዊ መንደሮች፣ 3 ሰው ሰራሽ ግድቦች፣ ለመንደሩ የሚያገለግል 13 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት ግንባታ እንዲሁም የውሃ፣ የመብራት እና የቴሌኮም መስረተ ልማቶች እንዳሉት ጠቅሰዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድልን  እና ለጅግጅጋ ከተማ መነቃቃትን ከመፍጠሩ ባለፈ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር ታስቦ መገንባቱን አስገንዝበዋል፡፡

ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ለጎረቤት ሀገራት ቱሪስቶች ተመራጭ መዳረሻ እንደሚሆንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጠርም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

በተለይም ከበርበራ እስከ ውጫሌ፣ ከጅግጅጋ እስከ ጅቡቲ በመሰራት ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ከሸቤልለይ ሪዞርት ጋር ተጣምረው ጅግጅጋ ከተማን ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ እንደሚያደርጓት ይጠበቃል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ  እየሰሩ ያሉ የፌዴራል እና የክልሉን አመራሮች እንዲሁም ተቋራጭ ድርጅቶችን ያመሰገኑት አቶ አደም÷ፕሮጀክቱ ከፍጻሜ እንዲደርስ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.