Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን ቀን ፕሬዚዳንት ታየ በተገኙበት እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን ቀን በስድስት ኪሎ ካምፓስ እየተከበረ ነው።

በመርሐ ግብሩ ከፕሬዚዳንት ታየ በተጨማሪ ሚኒስትሮች፣ በዩኒቨርሲቲው የተማሩ ምሁራን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተማሩና አሁን ላይ በተለያዩ የሥራ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ ምሁራንና ታዋቂ የኪነ- ጥበብ ሰዎችም በሥነ-ስርዓቱ ላይ ታድመዋል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ታየ÷በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ታሪክ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ አበርክቶ፣ ስምና ዝና እንዳለው አንስተዋል።

በረጅም ዓመታት ልምዱ በርካታ የምርምር ሥራዎችን በማበርከትና ምሁራንን በማፍራት የሀገር ባለውለታ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ያካበተውን ልምድ በሚመጥን መልኩ በትምህርት፣ በጥናትና ምርምር ሥራዎች ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን ለዩኒቨርሲቲያቸው የላቀ እድገት አሁንም አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው አንስተው÷በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት 74 ዓመታት በርካታ ምሁራንን ማፍራት መቻሉን አውስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የእውቀት ማዕከልነቱን ለማስቀጠል ራስ ገዝ ሆኖ በአዲስ መልክ በመደራጀት ዘመን ተሻጋሪ የትምህርት፣ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.