Fana: At a Speed of Life!

ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ሲጠቀሙና ሲያዘዋውሩ የተገኙ ግለሰቦች ላይ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ፖሊስ ገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ሲጠቀሙ እና ሲያዘዋውሩ አግኝቻቸዋለሁ ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን አዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አንደኛውን ሀሰተኛ ብር በመጠቀም ግዥ የፈፀመውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ያዋለው በክፍለ ከተማው ወረዳ 12 አካባቢ ነው፡፡

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ አስቀድሞ 400 ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ተጠቅሞ ግዥ ፈፅሞ ቢሰወርም ፖሊስ ባደረገው ክትትል በሌላ ቀን ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ሲፈፅም እጅ ከፍንጅ መያዙን መምሪያው አስታውቋል፡፡

በግለሰቡ መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራም 17 ሺህ 200 ሀሰተኛ የብር ኖት እንደተገኘ መገለፁን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

ፖሊስ ያሰባሰበውን ማስረጃ መሰረት በማድረግ ሁለተኛውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራውን ማስፋት ቀጥሎ ለሁለቱ ተጠርጣሪዎች ሀሰተኛ ገንዘብ የሚያከፋፍላቸውን ግለሰብ በቁጥጥር አውሎ በመኖሪያ ቤቱ ባደረገው ብርበራ 48 ሺህ 200 የኢትዮጵያ ብር እና 211 የኤርትራ ናቅፋ ይዟል፡፡

እንዲሁም ባለ 100 ብዛት 20 ሃያ እና ባለ 50 ኖት ብዛት 1 አንድ የአሜሪካ ዶላር፣ ባለ 1 ሺህ ኖት ብዛት 1 እና ባለ 500 ኖት ብዛት 1 የዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች ድርሀም፣ ባለ 500 ኖት ብዛት 1 የሳውዲ አረቢያ ሪያል ይዞ ምርመራውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

የተያዙት ገንዘቦች በሙሉ ሀሰተኛ መሆናቸውም መረጋገጡ ተነግሯል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.