Fana: At a Speed of Life!

የፖሊዮ በሽታ አጋላጭ ምክንያቶች እና መከላከያ መንገድ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣና በዋናነት የህፃናትን ጤና በመጉዳት እስከሞት የሚያደርስ በሽታ ነው፡፡

በሽታው በህፃናት ላይ የእጅ የእግር ወይም የሁለቱም መዛል (መዝለፍለፍ) ወይም ሽባነት ብሎም ሞት የሚያስከትል ነው፡፡

በአብዛኛው ህፃናትን በሚያጠቃው በዚህ በሽታ የተጠቁ ህፃናት ምልክቱ ላይታይባቸው ይችላል፡፡

ፖሊዮ ተላላፊ ሲሆን÷ የነርቭ ስርዓትን በመጉዳት ዘላቂ ለሆነ የአካል ጉዳትም ሊዳርግ ይችላል፡፡

የግል ንፅህናን አለመጠበቅ ማለትም እጅን በተገቢው መንገድ አለመታጠብ፣ ንፅህናው የተጠበቀ እና የተጣራ ውሃ አለመጠቀም፣ ምግብን አብስሎ አለመጠቀም እና የፖሊዮ መከላከያ ክትባት አለመውሰድ በበሽታው የመጋለጥ እድልን ያሰፋል፡፡

ለዚህም በዋነኝነት የሚሰጠውን የፖሊዮ መከላከያ ክትባትን ለልጆች ማስከተብና የግል ንፅህናን በአግባቡ መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡

አሁን ላይም አዲስ አበባን ጨምሮ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመስከረም ወር መጨረሻ ቀናት ጀምሮ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን በማስከተብ ሃላፊታቸውን እንዲወጡ ለሚመለከታቸው አካላት ጥሪ ቀርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.