በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አባቡ ዋቄ በዞኑ ሉሜ ወረዳ የዘንድሮውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በይፋ አስጀምረዋል፡፡
የማሳ ዝግጅት ስራ በዞኑ በሚገኙ 10 ወረዳዎች በ136 ቀበሌዎች ላይ እየተከናወነ እንደሚገኝ ዋና አስተዳዳሪው አመላክተዋል።
በዞኑ ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን እየተሰራ ሲሆን÷ እስካሁን ከ10 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መታረሱንና ከዚህም ውስጥ 6 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በዘር የመሸፈን ስራ መጀመሩን አቶ አባቡ ገልፀዋል።
የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ በበኩላቸው÷ ባለፉት ዓመታት በዞኑ የሚታረስ የመሬት ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ተናግረዋል።
በመራኦል ከድር