ኧርሊንግ ሃላንድ የኖርዌይ ብሄራዊ ቡድን የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኖርዌጂያኑ የማንቼስተር ሲቲ አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ በ36 ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ባስቆጠራቸው ግቦች የሀገሩ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለመሆን በቅቷል፡፡
የ24 ዓመቱ አጥቂ ትናንት ምሽት በአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ጨዋታ ኖርዌይ ስሎቫኒያን 3 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ 2 ግቦችን በማስቆጠር ሪከርዱን የግሉ ማድረግ ችሏል፡፡
ሃላንድ በአጠቃላይ በ36 ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች 34 ግቦችን በማስቆጠር ነው ለ90 ዓመታት በሀገሩ ልጅ ጆርገን ጁቬ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ያሻሻለው፡፡
በፈረንጆቹ 1920 እና 1930ዎቹ ሲጫዋት የነበረው ጁቬ 33 ግቦችን ለኖርዌይ ብሄራዊ ቡድን በማስቆጠር ሪከርዱን ይዞ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ሃላንድ ከጨዋታው በኋላ በሰጠው አስተያየት “ጥልቅ ኩራት ተሰምቶኛል ፤ ታሪክ ሰሪ በመሆኔም ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡
ተጫዋቹ በቀጣይ የሚያስቆጥረውን የግብ መጠን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ መናገሩንም ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡