በግብር አሰባሰብ ላይ አዎንታዊ ለውጦች እየታዩ ቢሆንም ጅማሮውን ማስቀጠል ይገባል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብር አሰባሰብ ላይ አዎንታዊ ለውጦች እየታዩ ቢሆንም ይህን ጥሩ ጅማሮ ማስቀጠል ይኖርብናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራ ትስስር ገጻቸው÷የ6ኛው የታማኝ ግብር ከፋዮች ሽልማት ተሸላሚዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የዜግነት ግዴታችሁን ለመወጣት ያደረጋችሁት ቁርጠኝነት ምስጋና የሚገባው ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡
ታማኝነት ከግለሰብ ይጀምራል፤ ግብር መክፈል ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን የዚያ እምነት መገለጫ ነው፤ ለበለጠ ጥቅም ሁላችንም የምንካፈለው ግዴታችን ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ለታማኝነታችሁ መንግስት የከፈላችሁት ግብር በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ለጋራ እድገታችን ወሳኝ በሆኑ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባሉ ግዙፍ የሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ አስተዋፅኦችሁን በማዋል ይህንን አደራ ያከብራል ነው ያሉት፡፡
በግብር አሰባሰብ ላይ አዎንታዊ ለውጦች እየታዩ ቢሆንም፣ ይህን ጥሩ ጅማሮ ማስቀጠል ይኖርብናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ሙስናን መቀነስ እና የግብር አሰባሰብ ሥርዓታችንን ማዘመን ለሁሉም የተመቸ፣ ግልፅ፣ ቀልጣፋ እና ፍትሃዊ አሰራር ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡