Fana: At a Speed of Life!

በምርቃቱ ዕለት ለእጮኛው ቀለብት ያሰረው ወታደር…

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የጊቤ ማሰልጠኛ በሁለት ዙር ለ4 ወራት ያሰለጠናቸውን ታክቲካልና ስልታዊ የሻምበል እና የሬጅመንት አመራሮች አስመርቋል፡፡

በወቅቱ ስልጠናውን በብቃት ያጠናቀቁ ሰልጣኞች በመድረክ አጋፋሪው አማካይነት ስማቸው እየተጠራ ተራ በተራ ወታደራዊ ሰላምታ እያቀረቡ የሽልማትና የሰርተፊኬት አሰጣጡ መካሄድ ጀምሯል።

ተራው ደርሶት ስሙ የተጠራው ተመራቂ አስር አለቃ ኤርሚያስ ሃይማኖት ለታዳሚዎች ወታደራዊ ሰላምታ ካቀረበ በኋላ በመድረክ አጋፋሪው አማካይነት ለእጮኛው የቃል ኪዳን ቀለበት ሊያደርግላት እንደሚሻ ገለጸ።

ከጓዶቹ ጋር ለምረቃ ዕለት የበቃው የ103ኛ ጊቤ ኮር አባሉ አስር አለቃ ኤርሚያስ ለወደፊት የትዳር አጋሩ ሳይታሰብ በምረቃው መድረክ የታገቢኛለሽ ጥያቄን አቀረበ።

የቀለበት ሥነ-ሥርዓቱም የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ዘውዱ በላይ እና የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት ተከናውኗል።

ጥንዶቹ በወጉ መሰረት የሽማግሌዎችን እና የአባገዳዎችን ጉልበት ስመው ጋብቻቸው ይባረክ ዘንድ ተመርቀዋል።

ኪሎ ሜትሮችን አቋርጣ ከምትኖርበት አምቦ ከተማ ተነስታ በምረቃው ላይ የታደመችው እጮኛው ወ/ሪት ቃልኪዳን ንጉሴ በዕለቱ ሌላ ምርቃት በደስታ ላይ ሌላ ዓለም እንደሚፈጠረ በፍጹም እንዳልገመተች ገልጻለች።

በውትድርና ዓለም ውስጥ ሆኖ ግዳጁን በብቃት ይወጣ ዘንድ፣ እናት ሀገሩን በታማኝነት እንዲያገለግል ሌላ ብርታት ለሆነችው ፣እርሱ ‘እናት’ ሲል የሚጠራት እጮኛው እንደሆነች በመድረክ ፍቅሩን ገልጿል።

ወ/ሪት ቃልኪዳን በውትድርና ሞያ ለመቀላቀል በተደጋጋሚ ሞክራ ባይሳካላትም ፣ አጋሯ በሞያው ጸንቶ ለሀገሩ ነጻነት እንዲቆም አይዞህ ባዩ ሆናለች።

እርሱ ተራርቀውም ቢሆን በውትድርናው አለም ግዳጁን በብቃት ይወጣ ዘንድ ላስቻለችው እጮኛው ክብር ሲል ይህን መድረክ እንደተጠቀመው ተናግሯል።

በወርቃፈራሁ ያለው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.