አቶ አህመድ ሺዴ ከቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ ልዑክ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህምድ ሺዴ በቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ ምክትል ሊቀመንበር ዣኦ ፌንግታኦ ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ አቶ አህመድ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰዳቸውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሮችንና ባለፉት ሁለት ወራት የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የቻይና መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመተግበር የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ እና ለኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በቡድን 20 አባል ሀገራት ማዕቀፍ መሰረት የእዳ ማራዘም እንዲደረግ እና በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ላሉ ፕሮጀክቶች አስቸኳይ የፋይናንስ ድጋፍ መደረግ እንዳለበት አንስተዋል፡፡
ዣኦ ፌንግታኦ በበኩላቸው÷ ተቋማቸው በቅርቡ የተመረጡ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በቀጣይም የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚን፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን፣ የግል እና የመንግስት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ እንዲሁም በሰብዓዊ ልማት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚሰሩ መግለፃቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።