በመኖሪያ ቤት ላይ የወደቀ ዛፍ እናትና የሁለት ወር ልጇን ሕይወት ቀጠፈ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ ከበርታ ቀበሌ ቆንጨልቃ መንደር የጣለውን ዝናብ ተከትሎ በመኖሪያ ቤት ላይ የወደቀ ዛፍ አንዲት እናት ከሁለት ወር ሕፃን ልጇ ጋር ሕይወታቸው አለፈ፡፡
በተመሳሳይ በወረዳው ቂጤ ቀበሌ ጋራ መንደር አካባቢ በወቅቱ እየጣለ ከነበረው ዝናብ ለመጠለል ዛፍ ሥር የነበረች ግለሰብ ዛፉ ወድቆባት ሕይወቷ ማለፉን የዞኑ ፖሊስ አስታውቋል።
እንዲሁም ቡና በመልቀም ላይ የነበሩ ሠራተኞች ዳስ ውስጥ እያሉ ዛፍ ወድቆባቸው በአንድ ሰው ላይ ከባድ እና በሰባት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል መባሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
ሕብረተሰቡ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ዛፍ ስር ከመጠለል እንዲቆጠብና በመኖሪያ ቤት አካባቢ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ዛፎች ካሉ በመቁረጥ እንዲያስወግድ የዞኑ ፖሊስ መክሯል፡፡