ከአዲስ መንጃ ፈቃድ እና ዕድሜያቸው ከ55 በላይ ከሆኑ ውጭ ሁሉም መንጃ ፈቃዶች ከነገ ጀምሮ በ4 ዓመት ይታደሳሉ – ባለሥልጣኑ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአዲስ መንጃ ፈቃድ እና ዕድሜያቸው ከ55 በላይ ከሆኑ ውጭ ሁሉም መንጃ ፈቃዶች ከነገ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአራት ዓመት እንደሚታደሱ የአዲስ አበባ አሽከርካሪና ተሸከርካሪ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ባለፉት 6 ዓመታት የመልካም አስተዳደር እና የፍትሐዊነት ጥያቄን ሲያስነሳ የነበረው የሁለት ዓመት እና የአራት ዓመት የመንጃ ፈቃድ ዕድሳት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ባለሥልጣኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አጋርቷል፡፡
በዚሁ መሠረትም ከአዲስ መንጃ ፈቃድ እና ዕድሜያቸው ከ55 በላይ ከሆነ ውጭ ሁሉም መንጃ ፈቃዶች ከነገ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአራት ዓመት የሚታደሱ ይሆናል ብሏል።
አዲስ መንጃ ፈቃድም ከሁለት ዓመት የሙከራ በኋላ ባለው አሰራር መሠረት በየአራት ዓመቱ ይታደሳል ነው የተባለው፡፡
ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑት ደግሞ በየሁለት ዓመት የሚታደስ ሆኖ÷ ክፍያው የአራት ዓመቱ ክፍያ ግማሽ (50 በመቶ) ይሆናል መባሉን የባለሥጣኑ መረጃ አመላክቷል፡፡