Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ ለአሻም ቴሌቪዥን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለአሻም ሚዲያ ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷አሻም ቴሌቪዥን የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ 1238/2013 እና ሌሎች የሀገሪቱ ሕጎችን እንዲሁም የፈቃድ ውል ግዴታዎችን አክብሮ ለመስራት ከባለስልጣኑ ፈቃድ ወስዶ በስርጭት ላይ እንደሚገኝ አንስቷል፡፡

ይሁን እንጂ ጣቢያው ትክክለኛ ያልሆነ መረጃዎችን ግጭት አባባሽ ዘገባዎችን፣ የሕዝብን አብነሮት የሚሸረሽሩና የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም የሚጎዱ መረጃዎችን በቂ ማጣራትና ምክንያታዊ ጥረት ሳያደርግ ተደጋጋሚ ማሰራጨቱን በይዘት ክትትል መረጋገጡ ተጠቁሟል፡፡

የቴሌቪዥን ጣቢያው ከዚህ ቀደም ባሰራጨው ግጭት ተኮር እና ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ ከድርጊቱ እንዲቆብ በተደጋጋሚ የጽሑፍና የቃል ማሳሰቢያ ሲሰጠው መቆየቱም ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂጣቢያው በባለስልጣኑ የተሰጠውን የጽሑፍና የቃል ማሳሰቢያ ባለማክበር የሀገሪቱን ሕጎች የሚጥሱ ይዘቶችን በማሰራጨት ላይ መሆኑን ነው ባለስልጣኑ የገለጸው፡፡

ጣቢያው ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ በየጊዜው የሚሰራጩ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ወደ መደበኛ ሚዲያ በማምጣት ኅብረተሰቡን ለማደናገር ጥረት ሲያደርግ እንደሚስተዋልም ተጠቅሷል፡፡

በመሆኑም ባለስልጣኑ አሻም ቴሌቪዥን በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ 1238/2013 መሰረት የሕግ የበላይነትን አክብሮ በገባው የፈቃድ ውል ግዴታ ከመስራት አንጻር በፈጸመው ተደጋጋሚ ጥሰት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መሆኑን አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.