19 የአፍሪካ ሀገራት የተሳተፉበት የዲጂታል ጤና መረጃ ሥርዓት ጉባዔ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የመጀመሪያውና በማህበረሰብ ጤና መረጃ ሥርዓት ላይ ያተኮረ ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ከ19 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ በዲጂታል ጤና ላይ የሚሰሩ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር አየለ ተሾመ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ የኤሌክትሮኒክስ የማህበረሰብ ጤና መረጃ ሥርዓት ለጤናው ዘርፍ ጉዞ ትልቅ ሚና ማበርከቱን አንስተዋል፡፡
በተለይም ለማህበረሰቡ፣ ለጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች፣ ለጤና ባለሙያዎች እና በየደረጃው ለሚሰሩ አመራሮች የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከ6 ሚሊየን በላይ አባወራ እና ከ25 ሚሊየን በላይ ቤተሠቦች በኤሌክትሮኒክስ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መረጃ ሥርዓት እንደሚታገዙ ተናግረዋል፡፡
የጤና ስርዓቱን በማዘመን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና አገልግሎቱን ወረቀት አልባ ለማድረግና የጤና አገልግሎቱን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ አንደሆነ መናገራቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፤፤
ሚኒስትር ዴዔታው የ“ኮም ኬር ሶሉሽን” ሶፍትዌር መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ጆናታን ጃክሰንንና ጉባዔውን በማስተባበር እገዛ ያደረጉ አጋር ድርጅቶችን እንዲሁም ተሳታፊዎችን አመስግነዋል።