ከመስከረም 28/2017 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በሥራ ላይ የሚውለውን የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የአገር በቀሉ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል የሆነውና ከሐምሌ ወር 2017 የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ በዓይነቱ ፤በንግድ ዘርፉ ውጤታማነት ላይ በሚያሳድረው በጎ ተፅእኖ እና በታሪካዊነቱ የተለየና ሥር ነቀል ማሻሻያ ነው፡፡
በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ላይ የተደረገው ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ ከሦስት አስርት አመታት በላይ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተከልሎ የቆየውና የውጭ ባለሀብቶች በገቢ፤ በወጪና በጅምላ የንግድ የሥራ መስኮች እንዲሣተፉ ለማድረግ ከተወሰደው የፖሊሲ ለውጥ ጋር ተቀናጅቶ ሲተገበር በዘርፉ ለበርካታ ዓመታት ማነቆ ሆነው የቆዩትን የግልፅነት፤የኢ-ፍትሃዊነትና የነፃ ውድድር ችግሮችን ከመሠረቱ ይቀርፋል ተብሎ ይታመናል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር በመንግሥት የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በገበያ ውስጥ የአቅርቦት መስተጓጓል እንዳይከሰትና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ባለፉት ወራት ከክልሎችና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት በተሠሩት የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች የተረጋጋ ግብይትና ዋጋ እንዲኖር አስችሏል፡፡
በገበያ ማረጋጋቱ ሂደት ጊዜያዊ ጥቅም ሳያማልላቸው ከመንግሥት ጎን በመቆም ለገበያ መረጋጋትና ለፖሊሲው ተፈፃሚነት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱት የንግዱ ማህበረሰብና የክልል አካላት ያለን አድናቆትና ምስጋና ከፍ ያለ ነው።
ምንም እንኳን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍ ያለ ጭማሪ ያስከተለ ቢሆንም የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባትና በመስከረም ወር የሚከበሩ ታላላቅ በዓላት በተረጋጋ ሁኔታ እንዲከናወኑ ለማድረግ ሲባል የነዳጅ ውጤቶች ዋጋ ከፖሊሲ ለውጡ በፊት በነበረበት መጠን እንዲቀጥልና የታየው ጭማሪ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ድጎማ እንዲሸፈን በመደረጉ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ መንግሥት ከብር 35 ነጥብ 8 ቢሊየን በላይ ወጪ አድርጓል።
በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያውን መነሻ በማድረግ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋባለመስተካከሉ በአገራችን በሥራ ላይ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከሁሉም ጎረቤት አገሮች በግማሽ ዝቅ ባለ መጠን የሚሽጥበት ሁኔታ በመጠፈሩ ነዳጅ በኮንትሮባንድና ለህገ ወጥ ንግድ እንዲጋለጥ አድርጓል፡፡
በእነዚህ መሠረታዊ ምክንያቶች ያለንበትን ሀገራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ አግባብ መጠነኛ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጓል፡፡ በዚህም መሠረት የኢኮኖሚውን ወቅታዊ ሁኔታና የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም እንዲሁም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ገበያ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ያገናዘበ የዋጋ ማስተካከያ ስትራቴጂ ተነድፎ ሥራ ላይ እንዲውል በመንግሥት ተውስኗል፡፡
በስትራቴጂው መሠረት በነዳጅ ዋጋ ላይ ከታየው ጭማሪ ተጠቃሚው ህብረተሰብ እጅግ አነስተኛ የሆነ ዋጋ በየሶስት ወሩ እየከፈለ፣ መንግሥት ደግሞ ከፍ ያለውን መጠን እደጎመ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የተሟላ የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግ ይሆናል፡፡
ይህ አሰራር በመንግስት ላይ ከፍተኛ ወጪ የሚያስከትል ቢሆንም የተረጋጋ ሽግግር በማድረግ በገበያ ላይ በገበያ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የሚኖረውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት የሚፈፀም ይሆናል፡፡
በዚሁ መሠረት የአለም የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ማስተካከያ በየሦስት ወሩ የሚደረግ ሲሆን መንግሥት ለአንድ ዓመት የሚቆይ ጥቅል ድጎማ ያደርጋል፡፡ የድጎማው መጠን በነዳጅ ዓይነት የሚለያይ ሆኖ የነጭ ናፍጣና የኬሮሲን በዋጋ ግንባታው በሥሌት በተደረሰበትና በሥራ ላይ ባለው ዋጋ መካከል ከሚኖረው ልዩነት እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን በየሶስት ወሩ ወደ ተጠቃሚው በማስተላለፍ ቀሪው ከ80 በመቶ ጀምሮ እየቀነሰ የሚሄድ መጠን በመንግሥት ጥቅል ድጎማ እየተደረገ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተሟላ የዋጋ ማስተካከያ ይደረጋል፤
የቤንዝንና የአውሮፕላን ነዳጅ በዋጋ ግንባታው በሥሌት በተደረሰበትና በሥራ ላይ ባለው ዋጋ መካከል ከሚኖረው ልዩነት እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን በየሶስት ወሩ ወደ ተጠቃሚው በማስተላለፍ ቀሪው ከ80 በመቶ ጀምሮ እየቀነሰ የሚሄድ መጠን በመንግሥት ጥቅል ድጎማ እየተደረገ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተሟላ የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግ ይሆናል፤
ሌሎች የነዳጅ ውጤቶችን (ቀላልና ከባድ ጥቁር ናፍጣ) በሥሌት የተደረሰበት ዋጋ ያለድጎማ በቀጥታ ወደ ተጠቃሚው እንዲተላለፍ ተወስኗል፤
በስሌት የተገኘው የቤንዚን ችርቻሮ ዋጋ በአዲስ አበባ ላይ ብር 117.28 በሊትር ሲሆን በሥራ ላይ ካለው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር የብር 34. 68 ወይም የ42.0 መቶኛ ጭማሪ አሣይቷል።
በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በመጀመሪያ ዙር በቤንዚን የችርቻሮ ዋጋ ላይ ከታየው ጭማሪ ብር 34.68 ውስጥ ተጠቃሚው ብር 8.54 በሊትር ወይም 24.60 በመቶ ብቻ እንዲከፍል የሚደረግ ሲሆን ቀሪው ብር 26.14 በሊትር ወይም 75.4 በመቶ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት በመንግሥት እየተደጎመ እንዲቀጥል የሚደረግ ይሆናል፡፡ ይህ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ የቤንዚን ዋጋ ብር 91.14 በሊትር ይሆናል ማለት ነው፡፡
የአውሮፕላን ነዳጅም ለቤንዚን በተደረገው የድጎማ መቶኛ መጠን የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በስሌት የተደረሰበት በነጭ ናፍጣ የችርቻሮ ዋጋ በአዲስ አበባ ላይ ብር 117.00 በሊትር ሲሆን በስራ ላይ ካለው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር የብር 33.26 በሊትር ወይም የ39.7 በመቶኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡በነጭ ናፍጣ ችርቻሮ ዋጋ ላይ ከታየው ከዚህ ጭማሪ ውስጥ ተጠቃሚው ብር 6.54 በሊትር ወይም 19.7 በመቶ ብቻ የሚከፍል ሲሆን ቀሪው ብር 26.72 በሊትር ወይም 80.3 በመቶ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት በመንግሥት እየተደጎመ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በዚሁ መሠረትበአዲስ አበባ ከተማ የነጭ ናፍጣ አዲሱ ዋጋ ብር 90.28 በሊትር ይሆናል ማለት ነው፡፡ የነጭ ናፍጣ
ዋጋን ከሌሎቹ የነዳጅ ዓይነቶች በበለጠ መደጎም ያስፈለገበት ምክንያት በትራንስፖርት ወጪ መናር ምክንያት የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት በማሰብ ነው፡፡ በነዳጅ ላይ የሚደረገው መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ በትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ላይ የሚያስከትለውን ጭማሪ ለማረጋጋት አግባብነት ያለው የታሪፍ ማስተካከያ የሚደረግ ሲሆን የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሠጡ አገር አቋራጭና የከተማ አውቶቡሶች ቀደም ሲል ሲደረግ የነበረው ድጎማም ባለበት የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በዚህ አግባብ ለሚደረግ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ መርሃ ግብር መንግሥት በሶስት ወራት ብቻ በአማካይ ብር 33.00 ቢሊየን የድጎማ ወጪ የሚከፍል ሲሆን የአለም ዋጋ አሁን ባለበት መጠን የሚቀጥል ከሆነ በአንድ ዓመት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ለነዳጅ ድጎማ ወጪ የሚያወጣ ይሆናል፡፡ እንዲሁም ቀደም በ2016 በጀት ዓመት በዱቤ ተገዝቶ ለተሸጠና ለአቅራቢዎች ክፍያውን በዚህ ዓመት ለመፈፀም የውጭ ምንዛሪ መግዣ የሚውል ተጨማሪ ብር 150 ቢሊዮን ወጪ በመንግስት የሚሸፈን ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ የፖሊሲ ለውጡን ተከትሎ ለነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ድጎማ ከብር 250.0 ቢሊዮን በላይ ወጪ የሚያደርግ ይሆናል፡
ሁሉ አቀፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋን ለማስተካከል መንግሥት እያደረግ ያለውን ጥረትና ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ህዝባችን ይገነዘባል የሚል ፅኑ እምነት ያለን ሲሆን በኢኮኖሚያችን ዘመናት ያስቆጠሩትን መዋቅራዊ ተግዳሮቶችና ህዝቡን ያማረሩና በንግድ ሥርዓቱ የሚሰተዋሉትን የግልፀኝነትና የፍትሃዊነት ችሮችን ለመቅረፍ ታስቦ እየተተገበረ የሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያው የታሰበለትን ግብ እንዲያሳካ የንግዱ ማህበረሰብና መላው ህዝባችን እንደከዚህ ቀደሙ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡ የፖሊሲ ለውጡን ተከትሎ ተደረገው የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ ተገን በማድረግ ምክንያታዊ ያልሆነና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን በአቅራቢያ ለሚገኙ የንግድ ፅህፈት ቤቶችና በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ጥቆማ መስጠት ሚቻል መሆኑን እናሳስባለን ፡፡
በተዘጋጀው የዋጋ ማስተካከያ ስትራተጂ መሠረት ይህ የመጀመሪያው ዙር የነዳጅ ውጤቶች የዋጋ ክለሣ ከዛሬ መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽቱ 12፡00 ሠዓት ጀምሮ ሥራ ላይ የሚውል ይሆናል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ የሚደረግ የነደጅ ውጤቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ