የሀገራችንን ብልፅግና የሚያስቀጥል ኃይል አፍርተናል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገራችንን ዕድገትና ብልፅግና ማስቀጠል የሚችል አስተማማኝ የሰላም ኃይል አፍርተናል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በቢሾፍቱ የዝግጁነት ማረጋገጫ ማዕከል በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተሟላ ጥገና ተደርጎላቸው በመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ተሻሽለው የተሠሩ የሰራዊቱን የግዳጅ አፈፃፀም የሚያሳልጡ የሜካናይዝድ ትጥቆችን ጎብኝተዋል።
በዚሁ ወቅትም ሰራዊታችን ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር የሚለውን የተቋሙን እሴት መሠረት በማድረግ ለሕይወቱ ሳይሳሳ መስዋዕትነት እየከፈለና ሰላምን እያረጋገጠ የሚገኝ የሕዝብ ዋልታና መከታ ነው ብለዋል፡፡
ተቋማችን የሚሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በእቅዳችን መሰረት ያለምንም እንቅፋት መወጣት የሚችል አስተማማኝ ኃይል አፍርተናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም የውስጥ አቅምን በመጠቀም ወጪ ቆጣቢነትን ባማከለ መልኩ የሰራዊታችንን የዝግጁነት ደረጃ ይበልጥ የሚያረጋግጡ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡
እነዚህ የዘመኑና የሰራዊታችንን የማድረግ አቅም በእጅጉ የሚያጎለብቱ ትጥቆች ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ተሻሽለው የተሰሩ ናቸው ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
ቀድሞ ወደነበሩበት የምስራቅ ዕዝ ሜካናይዝድ ክፍሎች ሲመለሱም የሠራዊታችንን ክንድ የሚያፈረጥሙ ተጨማሪ አቅሞች ይሆናሉ፡፡
በ2016 በጀት ዓመት በርካታ የተቋሙን ተልዕኮዎች በማቀድና በመምራት በኩል ከፍተኛ ስራ ለሰራው ለመከላከያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንና ለመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሰራዊታችንም በየጊዜው የሚታጠቃቸውን ትጥቆች በጥንቃቄና በእንክብካቤ በመያዝና በማቆየት እንዲሁም ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ በማዋልና እንደተቋምም የሀገራችንን እድገት በማስቀጠል በኩል የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ሰራዊቱም በትጥቅም ሆነ በስነ-ልቦናዊ ዝግጁነቱ ያለውን አቅም በማሳደግ እንደወትሮው ሁሉ ለሀገር ሰላምና ለሕዝብ ደኅንነት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡