Fana: At a Speed of Life!

የሳይበር ደኅንነት ወር ከጥቅምት 1 ቀን ጀምሮ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር አቀፉ የሳይበር ደኅንነት ወር ከመጪው ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር እንደሚካሄድ ተገለጸ።

ሀገር አቀፉ የሳይበር ደኅንነት ወር “የቁልፍ መሠረተ-ልማት ደኅንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 1ቀን ጀምሮ ለአንድ ወር እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ አምስተኛውን የሳይበር ደኅንነት ወርን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፤ የሳይበር ደኅንነት ወርን ማካሄድ ያስፈለገው ተቋማትና ዜጎች በዘርፉ ያላቸውን ንቃተ-ህሊና ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተቋማት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እያደገ በመምጣቱ፤ በዚሁ ሳቢያ የሳይበር ተጋላጭነት እንደሚጨምር አመላክተዋል።

በመሆኑም የሳይበር ወርን ማክበር የተቋማትንና የኅብረተሰቡን የሳይበር ደኅንነት ንቃተ-ህሊናን በማጎልበት ራሳቸውን እንዲከላከሉ ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በአገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆነ ቅንጅት በመፍጠር የሳይበር ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የሀገር አቀፉ የሳይበር ደኅንነት ወር ሲከበር በዘርፉ የሚደረጉ ውይይቶችና ምክክሮች፣ የተማሪዎች ውድድሮች፣ የ5 ሚሊየን የኮደርስ ኢኒሼቲቭ ለሳይበር ደኅንነት የሚጫወተው ሚና በሚል የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች እንደሚኖሩ ጠቅሰዋል።

አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ቁልፍ መሰረተ-ልማት የሚያስተዳድሩ ተቋማት፣ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እንደሚከፈት ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.