Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የሁለተኛው ምዕራፍ  የኮሪደር ልማት ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡

ከንቲባ አዳነች የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኮሪደርና የመልሶ ማልማት ስራ ዋና ዓላማ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብና ጽዱ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹና ማራኪ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ተወዳዳሪነት ማስቀጠል መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማው ብዙ አካባቢዎች እርጅና ተጭኗቸው ዜጎች ክብራቸውን በማይመጥን መልኩ እየኖሩ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም ገጽታዋን በእጅጉ መጉዳቱን ገልጸዋል።

የኮሪደርና መልሶ ማልማት በመጀመሪያው ምዕራፍ ስራ መለወጥ እንደሚቻል የታየበት ጠንካራ ትብብርና የስራ ባህል የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ቅድመ ዝግጅትን በተመለከተ ከነዋሪው ጋር ውይይት መደረጉንና በዚህም ስምንት ኮሪደሮችን የማልማት ስራ በዚህ ሳምንት እንደሚጀመር ገልጸዋል።

ለቀበሌ ቤት ተነሺዎች ምትክ ቤቶች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፤ይህም ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ከሚኖሩበት በእጅጉ የተሻለ መሆኑንና ለግል ቤቶችም አስፈላጊው ካሳ መዘጋጀቱን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

የተማሪዎች የመማር ማስተማር ስራም እንዳይስተጓጎል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውንም አክለው ገልጸዋል።

ተነሺዎች ያላቸው ማህበራዊ ትስስር እንዳይበተን በአንድ አካባቢ እንዲሰፍሩ ሰፊ ስራ መሰራቱን ከንቲባዋ አያይዘው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኮሪደር እና መልሶ ማልማት የሚከናወኑ ስራዎች ህዝብ በጋራ የሚጠቀምባቸው መሆኑን ጠቁመው የተለያዩ ቅሬታዎችን የሚስተናገዱበት ስርአት መዘጋጀቱንም አመላክተዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.