Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት የልሂቃን ሚና ምንድን ነው?

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ልሂቃን ስለሚኖራቸው ተሳትፎ የምክክር ኮሚሽኑ ከታች የተዘረዘሩትን ጉዳዮች አቅርቧል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ሂደት ከዲሞክራሲ ልምምዶች አንዱ እንደመሆኑ የብዙ ከዋኞችን ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡ ሂደቱ አሳታፊነትን እና አካታችነትን እንደ ቁልፍ መርሆዎቹ በመውሰድ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ሀሳብ እና ተሳትፎ ማረጋገጥ እንዲሚገባው የስነ-ምክክር መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡

ይህንንም መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሕብረተሰቡ በራሱ ችግር ላይ ራሱ ተመካክሮ መፍትሔን ማምጣት አለበት የሚል ጠንካራ አቋም አለው፡፡ በመሆኑም በሂደቱ ላይ ጉልህ ሚናን ሊጫወቱ የሚችሉ አካላት በሂደቱ ኮሚሽኑ ባዘጋጀው ስነ-ዘዴ መሰረት ተሳታፊ እንዲሆኑ መንገዱ ተመቻችቷል፡፡

ስነ-ዘዴው ጉልህ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከሚያደርጋቸው አካላት መካካል ልሂቃን ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ልሂቃን በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ እንዴት እንደሚሳተፉ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ጥያቄን ሲፈጥር ተስተውሏል፡፡

በተለምዶው ልሂቃን ተብለው የሚጠሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች በሕብረተሰቡ ዘንድ ተፅዕኖን በመፍጠር በተለያየ ደረጃ ሊገለፅ የሚችል ቦታ የያዙ ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በብዙ መደብ ውስጥ ተበታትነው ይገኛሉ፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ያለፉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየን ሀገራቱ ሂደቱን ሲያከናውኑ በተለያየ ደረጃ የሚገለፁ ልሂቃንን ማሳተፋቸው ነው፡፡ ከእነዚህ ልሂቃን መካከል የፖለቲካ ልሂቃን፣ የኢኮኖሚ ልሂቃን፣ የማሕበራዊ ልሂቃን፣ ወታደራዊ ልሂቃን እና የመገናኛ ብዙሃን ልሂቃን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በሂደቱ የእነዚህን ልሂቃን ተሳትፎ እና ስብጥር በአግባቡ ጥቅም ላይ ያዋሉ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውጤታማ ከመሆናቸው ባሻገር ለሌሎች ሀገራት ልምድን ትተው አልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በምክክር ሂደቱ ውስጥ በርካታ የሚባሉ ባለድርሻ አካላትን እያሳተፈ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የልሂቃን ተሳትፎ አንዱን እና ዋናውን ቦታ ይዟል፡፡

ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ተሳታፊ የሚሆኑ ወኪሎችን ከየሕብረተሰብ ክፍሉ ሲያስመርጥ ማሕበራዊ ልሂቃንን በተሳታፊነት ብሎም በተባባሪ አካላትን እንደየአካባቢው ዓውድ ሲያሳትፍ ቆይቷል (የሃይማኖት መሪዎች፣ የማሕበረሰብ መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ቃዲዎች፣ የጎሳ መሪዎች ወዘተ)፡፡

በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ላይ ጉልህ ሚናን ሊጫወቱ የሚችሉ ከዋኞችም በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከወረዳ ጀምሮ ሲከናወን በነበረው እና በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ወኪሎችን በማስወከሉ ሂደት ላይ የንግድ ማህበረሰቡን በመወከል የተለያዩ ተወካዮች መዋቅሮቻቸውን በመጠቀም ሲሳተፉ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ በአሁኑ ሰዓት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በሚያከናውንበት ወቅት በክልል/ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ባላቸው መዋቅር የንግድ ማህበራት ምክር ቤትን፣ የአሰሪዎች ማህበራትን እና የሰራተኞች ማህበራትን ተሳታፊ እያደረገ ይገኛል፡፡

እነዚህ ከዋኞችም በኢኮኖሚው ላይ ጉልህ ሚና እንዳለቸው ይታመናል፡፡ በመሆኑም በሂደቱ ጎምቱ ሊባሉ የሚችሉ እና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች በዚህ መዋቅር ውስጥ ተሳታፊዎች እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል የፖለቲካ ልሂቃን ሂደቱ በሚጋብዘው መሰረት በተለያዩ ደረጃዎች ተሳታፊ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡ አካታችነት እና አሳታፊነትን ለማስጠበቅም ኮሚሽኑ በክልሎች በሚያከናውነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ክልል አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፖርቲዎችን በማሳተፍ እና በፖለቲካው ምህዳር ላይ ያገባናል የሚሉ ተወካዩችን በመሰብሰብ መልካም ውጤቶችን ለማስመዝገብ እየሰራ ይገኛል፡፡

ወታደራዊ ልሂቃንም ሌሎቹ በሂደቱ ሊሳተፉ የሚገባቸው አካላት ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ የቀድሞ ሰራዊት አባላት እና በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ጥሪ እየቀረበላቸው ሲሆን ይህም ወታደራዊ ልሂቃን በሂደቱ የሚኖራቸውን ሚና በመረዳት ነው፡፡

ለሀገራዊ ምክክር ሂደት መሳካት የሚዲያ አካላት የጎላ ሚና ቀላል ቦታ የሚሰጠው አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደትም ሀገራዊ እና ክልላዊ የሚዲያ ተቋማት እና ባለሙያዎች ተሳታፊዎች እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ከላይ የተጠቀሱት የልሂቃን ስብስቦችን ማሳተፉ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚከናወኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች በየአካባቢው ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በማሳተፍ በሂደቱ ተገቢውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ በመጋበዝ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በተለያዩ የስራ ዘርፎች አንቱታን ያተረፉ እና ተዓማኒነት ያላቸው ግለሰቦች ይሳተፍሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ኮሚሽኑ የምሁራንን ሀሳብ እና ድምፅ ለመስማት እድሉን አመቻችቷል፡፡ በመሆኑም በሁሉም የሀገራችን ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምርት ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ መምህራን ስለሀገራቸው ጉዳይ ያላቸውን ሀሳቦች በተወካዩቻቸው በኩል እንዲያቀርቡ እና በክልሎች/ ከተማ አስተዳደሮች በሚዘጋጀው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ በኮሚሽኑ አሰራር ጥሪ እየቀረበላቸው ይገኛል፡፡

በቀጣዮቹ ጊዜያትም የምሁራንን ሀሳብ በተሻለ መልኩ ለመስማት እና የሂደቱ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ለማድረግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኮንሶርቲየም ጋር በመተባባር እየሰራ ይገኛል፡፡

በመጨረሻም ኮሚሽኑ በርካታ የሚባሉ ውይይቶችን ከባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ ኮሚሽኑ በተከተላቸው የአሰራር ስርዓቶች ውስጥ አልተካተትንም የሚል ቅሬታ ያላቸው አካላት ካሉ ኮሚሽኑ ሀሳባቸውን ለማስተናገድ ሁሌም በሩ ክፍት እንደሆነ ያሳውቃል፡፡

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.