የቡና ጥራትን በማሻሻል የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡና ጥራት ደረጃን በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር ገለጹ፡፡
ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ቡናን በኩታ-ገጠም የማምረት እና ያረጁ የቡና ተክሎችን የመጎንደል ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸው÷ አሁን ላይ ምርት መስጠት መጀመራቸውን አቶ ሻፊ ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመትም 326 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ መያዙን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግ የተሠራው ሥራ አመርቂ ቢሆንም ከጥራት አንጻር ግን መሻሻል የሚገባው መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ቡና ጥራት 1ኛ ደረጃ 13 በመቶ ብቻ ሲሆን÷ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የጥራት ደረጃ 4ኛ እና 5ኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን ቡና የጥራት ደረጃ ወደ 1ኛ እና 2ኛ ከፍ በማድረግ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህም አንጻር የቡና አብቃይ አካባቢዎች ከጥራት አንጻር ያሉበትን ደረጃ በመለየት ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡