ሩሲያ በኢትዮጵያ ት/ቤት የመክፈት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሸን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በሩሲያ ሴናተር ኒኮላይ ቪላዲሚሮቭ ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
አቶ አገኘሁ ኢትዮጵያና ሩሲያ የረጅም ዘመን የታሪክና የባህል ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው÷የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ሁለቱ ም/ቤቶች የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ መፈራረማቸውና ስምምነቱ ፈጥኖ ወደ ተግባር እንዲገባ የፌዴሬሽን ም/ቤት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ምክር ቤቱ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አያያዝ ዙሪያ ከሩሲያ ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአቅም ግንባታ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሩሲያን ድጋፍ እንደማይለያት ጠቅሰው÷በብሪክስ አባል ሀገራት የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ ተግታ እንደምትሰራ ጠቁመዋል፡፡
የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ የኢትዮጵያ ምኞት እንደሆነም ተናግረዋል።
የሩሲያው ሴናተር ኒኮላይ ቪላዲሚሮቭ በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሩሲያ ጠንካራ ወዳጅ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ሩሲያ በትምህርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በባህል ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልና የሩሲያን ት/ቤት በኢትዮጵያ የመክፈት ፍላጎት እንዳላት አንስተዋል።
ሩሲያ የብሪክስ አባል ሀገራት ሰብሳቢ በመሆኗ አባላቱ በትብብርና በቅንጅት እንዲሰሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደምታደርግ መናገራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።