በአማራ ክልል ከነገ ጀምሮ የፖሊዮ ክትባት ይሰጣል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ከመስከረም 27 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በዘመቻ እንደሚሰጥ የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንዳስታወቁት÷ ክትባቱ የሚሰጠው እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሁሉም ህጻናት ነው።
ፖሊዮ(የልጅነት ልምሻ) በሽታ በተበከለ ምግብና ውሃ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ በሽታ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በሽታው ዘላቂ ለሆነ የአካል ጉዳትና አልፎም ለሞት የሚዳርግ እንደሆነ ገልፀዋል።
ክትባቱ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች እንደሚሰጥ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ክትባቱን ከ4 ሚሊየን ለሚበልጡ ህፃናት ለመስጠት መታቀዱንና ህብረተሰቡ ከወዲሁ ተዘጋጅቶ መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ክትባቱ ቤት ለቤት፣ በትምህርት ቤቶች እና በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ለዘመቻው ውጤታማነት ወላጆች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለህዝቡ ግንዛቤ በመፍጠር ሚናቸውን እንዲወጡ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ክትባቱ ከዚህ ቀደም መደበኛ ክትባት ለወሰዱም ሆነ ላልወሰዱ ህጻናት የሚሰጥ መሆኑንና ክትባቱን ለሚሰጡ ባለሙያዎችና አስተባባሪዎች ተገቢ ስልጠናና ስምሪት መሰጠቱን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።