ሆረ አርሰዲ ኢሬቻ በቢሾፍቱ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ)የ2017 ሆረ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት መከበር ጀምሯል፡፡
በዓሉ “ኢሬቻ ለባህላችን ሕዳሴ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡
በአከባበር ሥነ-ሥርዓቱ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም ዞኖች የመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡
አሁን ላይ የበዓሉ ታዳሚዎች በአባገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች እየተመሩ በዓሉ የሚከበርበት ሆረ አርሰዲ ሐይቅ እየደረሱ ነው።
የበዓሉ ታዳሚዎች የኦሮሞ ሕዝብን ባሕልና ማንነት በሚያንጸባርቁ አልባሳትና ጭፈራዎች ታጅበው በዓሉን በድምቀት እያከበሩ ይገኛሉ።
ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁ ሁሉን ነገር ለፈጠረ አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበትና መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪን የሚለመንበት በዓል ነው።
በመላኩ ገድፍ