አቶ አወል አርባ የሰመራ ከተማን ምቹና ፅዱ ለማድረግ አመራሩ የድርሻቸውን እንዲወጣ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰመራ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹና ፅዱ ለማድረግ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ አሳሰቡ።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የሰመራ ከተማ የኮሪደር ልማትን እና የኮደርስ ስልጠና ኢንሼቲቭን አስመልክቶ ተወያይተዋል።
በውይይት መድረኩም ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰመራ ከተማን ምቹና ፅዱ ለማድረግ በሚከናወኑ ስራዎች ሁሉም የክልሉ ከፍተኛ አመራር በቁርጠኝነት ሀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አህመድ ኑር (ኢ/ር) በሰመራ ከተማ በ2017 ሊተገበር የታሰበውን የኮሪደር ልማትን በተመለከተ ባቀረቡት ዕቅድ፤ የከተማዋን የኮሪደር ልማት ለመተግበር ከአዲስ አበባ ልምድ ተወስዷል ብለዋል።
በዚህም መሰረት በሰመራ ከተማ በአራት ዙር 13 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮሪደር ልማት ለማከናወን መታቀዱን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ የዲዛይን ስራ 95 በመቶ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።
የኮደርስ ስልጠና ኢኒሼቲቭን በተመለከተ በተደረገው ውይይትም ስልጠናው በክልሉ በቴክኖሎጂ የዳበር ትውልድ በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ሁሉም የእድሉ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት መመላከቱን የአፋር ቲቪ ዘግቧል።