ተመድ ከ200 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን ወደ ሶሪያ መሰደዳቸውን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሊባኖስ እየተፈጸመ ያለውን የእስራዔል የአየር ጥቃት በመሸሽ ከ200 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን ወደ ሶሪያ መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግስታ ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ።
የተመድ የስደተኞች ከሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ፤ ከሊባኖስ ወደ ሶሪያ የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር 300 ሺህ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
እስራዔል የሂዝቦላህ የጦር ካምፖችን እና አመራሮችን ኢላማ በማድረግ እያከሄደች ባለው የአየር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ማጠናከሯን በመግለፅ የታጣቂ ቡድኑን አቅም ሳታዳክም ጥቃቱን እንደማታቆም በማስታወቋ የቀጣናው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
23 የሚጠጉ ሀገራት እየከፋ ባለው ጦርነት ሳቢያ ዜጎቻቸውን ከሊባኖስ ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ሲሆን፤ የንግድና ወታደራዊ አውሮፕላኖች በመጠቀም ዜጎቻቸውን ለማስወጣት እየሞከሩ ነው።
ብሪታኒያ በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎቿን ቻርተር አውሮፕላኖችን በመጠቀም እያስወጣች እንደምትገኝ ቢቢሲ ዘግቧል።
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ወደ ሊባኖስ በመላክ 97 የሚሆኑ ዜጎቿን ከሀገሪቱ ማስወጣት ችላለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሂዝቦላህ ሮኬት በማስወንጨፍ የእስራዔልን የራማት ዴቪድ አየር ማረፊያን መምታቱን የገለጸ ሲሆን እስራዔል ደግሞ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ በርካታ የሂዝቦላህ ተዋጊዎችን መግደሏን ገልጻለች።