ርዕሰ መሥተዳድር ዓለሚቱ ሕዝቡ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እንዲረባረብ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ አሳሰቡ።
ርዕሰ መሥተዳድሯን ጨምሮ የኑዌር ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ተወካዮችና አመራሮች የተሳተፉበት ሕዝባዊ ውይይት በላሬ ወረዳ ኮርጋንግ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ሕብረተሰቡ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት ርዕሰ መሥተዳድሯ አሳስበዋል፡፡
አስተማማኝ ሰላም ከሌለ ሕብረተሰቡ ሠርቶ መግባት እንደማይችል በመገንዘብ ሁሉም የሰላም እሴቶችን በማጎልበት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
ሰላምን በዘላቂነት ማስቀጠል የሚቻለው ያሉንን ስጋቶች ስናስወግድና አንድነታችንን ስናጠናክር ነው ማለታቸውን የክልሉ ከሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በክልሉ በነበረው ግጭት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡
በቀጣይም ፊታችንን ወደ ልማት በማዞር ክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች በመጠቀም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እንሠራለን ነው ያሉት፡፡