Fana: At a Speed of Life!

የፊታችን ሰኞ የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት  4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 58 ንዑስ አንቀፅ (2) እና  በምክር ቤቱ  የአሠራርና  የአባላት  የሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 24 ንዑስ አንቀፅ (1) መሰረት÷ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ዓመት የሥራ ጊዜ  ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ መሆኑ ተደንግጓል፡፡

በድንጋጌው መሰረት የ6ኛው ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የተጠናቀቀ ሲሆን÷ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓትም የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት በተገኙበት መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሠዓት ጀምሮ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ለሁለቱ የፌደራል መንግሥት ምክር ቤቶች ዓመታዊ  ሥራቸውን መጀመራቸውን በማብሰር የፌደራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ ያቀርባሉ።

የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው  ተጋባዥ እንግዶች በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሚገኙም ተጠቁሟል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.